-46-777-0614 info@sptc.edu.et Sawla, Gofa Zone, Ethiopia
🇬🇧 English 🇪🇹 አማርኛ

የሳውላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የክላስተር ኮሌጆች የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር እና የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡


(ሳውላ፣ ሰኔ 12/2018 ዓ.ም)
ሳውላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከክላስተር ኮሌጆች ጋር በመተባበር “በቴክኖሎጂ እንቅደም ወደ ስኬት እንድረስ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር እና የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
ፕሮግራሙን በይፋ የከፈቱት የሳውላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ጊንዳ ባህሩ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዋና ተልዕኮ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ማፍራት፣ ተግባራዊ የምርምር ውጤቶችን ማመንጨት እና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ፈጠራዎችን ማበረታታት በመሆኑ፣ ይህ ውድድርና ኤግዚቢሽን የኮሌጆችን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳየትና የልምድ ልውውጥን ለማጠናከር አስፈላጊ መድረክ መሆኑን ገልጸው ፕሮግራሙን በይፋ ከፍተዋል።
የፕሮግራሙ ዓላማ በክላስተር ኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ አሠልጣኞች፣ ተማሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች ያፈሯቸውን ፈጠራዊ ቴክኖሎጂዎች፣ ተግባራዊ የምርምር ውጤቶች እና ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ፣ የልምድ ልውውጥን ለማጎልበት እና የፈጠራ ባህልን ለማጠናከር ነበር።
በውድድሩ እና ኤግዚቢሽኑ ላይ ከተለያዩ ክላስተር ኮሌጆች የቀረቡ ቴክኖሎጂዎች እና የምርምር ሥራዎች በዳኞች በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ተገምግመው አሸናፊዎች ተለይተዋል። የቀረቡት ሥራዎች የቴክኖሎጂ ፈጠራን፣ ተግባራዊነትን እና ለማህበረሰቡ ችግር መፍትሔ የመስጠት አቅማቸውን በግልጽ ሁኔታ አሳይተዋል።
በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ እና የኮሌጁ ምክትል ዲን ተወካይ አቶ መሳይ ባህሩ ባደረጉት ንግግር፣ በፕሮግራሙ የታዩ ፈጠራዎችና የምርምር ውጤቶች የኮሌጆችን እየተሻሻለ የመጣ የቴክኖሎጂ አቅም እንደሚያሳዩ ገልጸው፣ ወደፊትም ተቋማት በጋራ በመሥራት ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍራትና ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ለፕሮግራሙ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ ክላስተር ኮሌጆች፣ አሠልጣኞች፣ ዳኞች፣ አጋር አካላት እና የኮሌጁ ማህበረሰብ ምስጋና አቅርበው ፕሮግራሙን በይፋ ዘግተዋል።
Website: https://www.sptc.edu.et/
Facebook: Sawla Polytechnic