እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ!
እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ!
ውድ የሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቤተሰቦች፣ የኮሌጃችን ተማሪዎች፣ አሰልጣኞችና ሠራተኞች፣ ወላጆች፣ የኢንዱስትሪና የሥራ ዓለም አጋሮቻችን፣ የአካባቢያችን ማህበረሰብ እንዲሁም ለኮሌጃችን ልማት እና እድገት አስተዋፅኦ ለምታደርጉ ሁሉ፤
በመጀመሪያ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም፣ በጤናና በደስታ አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ። አዲሱ ዓመት ለእያንዳንዳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ የሰላም፣ የጤና፣ የተስፋ፣ የብልጽግናና የስኬት ዓመት እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ። ያለፈው ዓመት ለእኛ የትምህርትና የሙያ ስልጠና ሥራችንን ለማጠናከር፣ የተማሪዎቻችንን ብቃት ለማሳደግ፣ ከኢንዱስትሪና ከሥራ ዓለም ጋር ያለንን ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም የኮሌጃችንን የጥራት ሥርዓት ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን የሠራንበት ዓመት ነበር። ለዚህ ሁሉ ስኬት የኮሌጃችን ማህበረሰብ ያሳየውን ትብብር፣ ትጋትና ቁርጠኝነት ከፍ አድርጌ አደንቃለሁ።
የኢትዮጵያ የቴክኒክና የሙያ ስልጠና ስትራቴጂ በጥራትና በተግባር የተመሠረተ ስልጠናን፣ ከሥራ ገበያ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የሙያ ብቃትን፣ የሥራ ዝግጁነትን፣ ሥራ ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ ምርምርና ፈጠራን እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጋር የተጠናከረ ትስስርን በአጽንኦት ያስቀምጣል። ይህ ስትራቴጂ የTVT ተቋማት ተማሪዎችን ብቻ የሚያሰለጥኑ ተቋማት ሳይሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማህበረሰብና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክቱ፣ የሚያድሱ፣ የሚያመነጩና የሚያስተላልፉ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ማዕከላት እንዲሆኑ ያበረታታል።
ስለዚህ ሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም በአዲሱ ዓመት ከዚህ ሀገራዊ አቅጣጫ ጋር በማጣጣም ብቁ፣በፈጠራ ክህሎት የተካኑ፣ ሥራ ፈጣሪ፣ ተለዋዋጭ የሥራ ዓለምን ለመቋቋም የተዘጋጁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ያጠናክራል። በተለይም ስልጠናችን ከኢንዱስትሪ ፍላጎትና ከሥራ ገበያ ጋር እንዲጣጣም፣ ተማሪዎቻችን ከቲዎሪ ባለፈ በተግባር የተመሠረተ ብቃት እንዲያገኙ፣ የኢንዱስትሪ ትስስርን፣ የሥራ ላይ ስልጠናን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ ምርምርና ፈጠራን እና የሥራ ፈጠራ ባህልን የበለጠ ለማጠናከር በጋራ እንሰራለን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኮሌጃችን ISO 21001:2025 የትምህርት ተቋማት የአስተዳደር ሥርዓት (Educational Organizations Management System-EOMS) ትግበራን በቁርጠኝነት እያስፋፋ ይገኛል። ለእኛ ISO 21001:2025 የምስክር ወረቀት ለማግኘት ብቻ የምንተገብረው ሥርዓት አይደለም። የጥራት ባህልን በኮሌጃችን ውስጥ ለመገንባት፣ ተማሪን ማዕከል ያደረገ አገልግሎትን ለማጠናከር፣ የሥራ ሂደቶችን ለማሻሻል፣ ተጠያቂነትን ለማሳደግና ቀጣይነት ያለው መሻሻልን የእለት ተዕለት የሥራ ባህላችን ለማድረግ የምንጠቀምበት መሣሪያ ነው።
ውድ የኮሌጃችን ቤተሰቦች፤ አዲሱ ዓመት የተሻለ የምንሠራበት፣ የበለጠ የምንማርበት፣ የምንፈጥርበት፣ጅማሬዎቻችንን አጠናክረን የምናስቀጥልበት ዓመት ይሁንልን። እንደ ኮሌጅ መሪ በእናንተ ትብብር፣ በችሎታችሁና በቁርጠኝነታችሁ ሙሉ እምነት አለኝ። በጋራ ከሰራን የሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን የተሻለ የትምህርት፣ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራና የኢንዱስትሪ ትስስር ማዕከል ማድረግ እንችላለን።
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
አዲሱ ዓመት ለእያንዳንዳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁና ለመላው የኮሌጃችን ማህበረሰብ የሰላም፣ የጤና፣ የብልጽግና፣ የእድገትና የታላቅ ስኬት ይሁን።
መልካም አዲስ ዓመት!
አቶ ጊንዳ ባህሩ
ሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን
2019 ዓ.ም